2 Chronicles 10

እስራኤል በሮብዓም ላይ ዐመፀ

10፥1–11፥4 ተጓ ምብ – 1ነገ 12፥1-24 1እስራኤላውያን ሁሉ ሊያነግሡት ወደዚያ ሄደው ስለ ነበር፣ ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2ከንጉሥ ሰሎሞን ሸሽቶ በግብፅ ይኖር የነበረው የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ይህን ሲሰማ፣ ከግብፅ ተመልሶ መጣ። 3እርሱንም ልከው አስጠሩት፤ ከዚያም እርሱና እስራኤል ሁሉ ወደ ሮብዓም ሄደው እንዲህ አሉት፤ 4“አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን አስጨናቂውን ሥራና በላያችን የጫነብንን ከባድ ቀንበር አቅልልልን፤ እኛም እንገዛልሃለን።”

5ሮብዓምም፣ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ወደ እኔ ኑ” አላቸው፤ ስለዚህ ሰዎቹ ወጥተው ሄዱ።

6ከዚያም ንጉሥ ሮብዓም፣ “ለዚህ ሕዝብ ምን እንድመልስለት ትመክሩኛላችሁ?” በማለት አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ ያገለገሉትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠየቃቸው።

7እነርሱም፣ “ለዚህ ሕዝብ ደግ ከሆንህለት፣ ደስ ካሰኘኸውና የሚስማማው መልስ ከሰጠኸው ምንጊዜም ይገዛልሃል” አሉት።

8ሮብዓም ግን ሽማግሌዎች የሰጡትን ምክር ትቶ፣ አብሮ አደጎቹና አገልጋዮቹ ከሆኑት ወጣቶች ምክር ጠየቀ፤ 9እንዲህም አላቸው፤ “ ‘አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን’ ለሚሉኝ ለእነዚህ ሰዎች የምትሰጡኝ ምክር ምንድን ነው? ምንስ ብለን እንመልስላቸው?”

10አብሮ አደጎቹም ወጣቶች እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “ለጠየቍህ ሕዝብ፤ ‘አባትህ በላያችን ከባድ ቀንበር ጫነብን፤ አንተ ግን ቀንበራችንን አቅልልልን’ ለሚሉህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ትንሿ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ይልቅ ትወፍራለች፤ 11አባቴ ከባድ ቀንበር ጫነባችሁ፤ እኔ ግን የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ።’ ”

12ንጉሡ፣ “ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሳችሁ ኑ” ባላቸው መሠረት ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ ሮብዓም ተመለሱ። 13ንጉሡም የሽማግሌዎችን ምክር በመናቅ፣ አመናጭቆ መለሰላቸው፤ 14እርሱም የወጣቶቹን ምክር በመቀበል፣ “አባቴ ቀንበራችሁን አከበደ፤ እኔ ደግሞ የባሰ አከብደዋለሁ፤ አባቴ በዐለንጋ ገረፋችሁ፤ እኔ ደግሞ በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” አላቸው። 15እግዚአብሔር በሴሎናዊው በአሒያ አማካይነት ለናባጥ ልጅ ለኢዮርብዓም የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣ ወስኖ ስለ ነበር፣ ንጉሡ ሕዝቡን አላዳመጠም።

16መላው እስራኤልም ንጉሡ ሊሰማቸው አለመፈለጉን በተረዱ ጊዜ፣ እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤

“ከዳዊት ምን ድርሻ አለን?
ከእሴይስ ልጅ ምን ክፍል አለን?
እስራኤል፣ ሆይ፤ ወደ ድንኳንህ ተመለስ፤
ዳዊት ሆይ፤ አንተም የገዛ ቤትህን ጠብቅ።”
ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ ወደየቤታቸው ተመለሱ።
17ይሁን እንጂ በይሁዳ ከተሞች የሚኖሩትን እስራኤላውያን አሁንም የሚገዛቸው ሮብዓም ነበር።

18ንጉሥ ሮብዓም የገባሮች ኀላፊ የነበረውን አዶራምን ላከው፤ እስራኤላውያን ግን በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሥ ሮብዓም ግን እንደ ምንም ብሎ ሰረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሽቶ አመለጠ። 19ስለዚህ እስራኤል እስከ ዛሬ ድረስ በዳዊት ቤት ላይ እንደ ዐመፀ ነው።

Copyright information for AmhNASV